ረቡዕ 26 ጁን 2013

የረመዳን ወር የትኩረት አቅጣጫዎች

የረመዳን ወር የትኩረት አቅጣጫዎች

1. ልቦናዎች የሚደብቁትን ሁሉ የሚያየውና የሚያውቀው አላህ (ሱ.ወ) የኢማናችንን ጥንካሬ በዚህ ፆም ሊፈትነን እንደፈለገ በመገንዘብ ከፍተኝ ትኩረት መስጠት፤
2. ረመዳንን ስንፆም በኒያ (አስበንና ወስነን) መሆን አለበት፤ ምክንያቱም ያለ ኒያ የፆመ ሰው ምንዳ የለውምና።
3. ቀኑን በሙሉ በመኝታ ከማሳለፍ መቆጠብ አለበን።
4. ቁርኣንን ከሌላው ጊዜ በተሻለ በብዛት መቅራት አለብን።
5. ከፈጣሪያችን ጋር ተውባ (ወደሱ መመለስ) ማደስ ያስፈልጋል።
6. የረመዳንን ሌሊቶች በጫወታና ጠቃሚ ባልሆኑ ነገሮች ከማሳለፍ መቆጠብ አለብን።
7. በረመዳን ወር ዱዓ፣ ከአላህ ማህርታ መጠየቅና ወደሱ መዋደቅ ማብዛት አለብን።
8. አምስት ወቅት ሶላቶችን በመስጂድ ጀመዐ ጠብቀን መስገድ ያስፈልጋል።
9. ሙሉ አካላችን አላህ (ሱ.ወ) ከከለከላቸው ነገሮች በመቆጠብ መፆም ይኖርባታል።

ቁርኣን የወረደበት የረመዳን ወር ይህ ነው፤ ይህ ወር ከጀነት የሚቀረብበትና ከእሳት የሚራቅበት ጊዜ ነው። እድሜህን ሁሉ ያለ ኢባዳ ያባከንክ፣ በረመዳንና በሌላውም ጊዜ ከኢባዳ ወደ ኋላ የቀረህ፣ዛሬ ነገ እያልክ በቀጠሮ ወደ አላህ መመለስን ያዘገየህ፣ ረመዳንንና ቁርኣንን በቸልተኝነት እያለፍክ ያለህ ሰው ሆይ! እስኪ በአላህ ይሁንብህ ንገረኛ እስከመቼ በንዲህ አይነት ህይወት ትቀጥላለህ? አይቀሬው ሞት ድንገት ከተፍ ቢል ጌታህፊት ምን ይዘህ ትቀርባለህ?... ከወዲሁ ቆም ብለህ ልታስብበት ይገባል!

በተከበረው ረመዳን ከምግብ ብቻ ተከልክለህ አይንህን፣ አንደበትህንና አጠቃላይ ውሎህን ያልገራሀው ወንድሜ ሆይ! ድካምህ በከንቱ እንዳይቀር እያሰብክበት ነውን? ስንት ፆመኛ አለ ከፆሙ ራሀብንና ጥምን እንጅ የማያተርፍ! ስንት ሰጋጅ አለ ከሶላቱ እንቅልፍ ማጣትና ድካምን እንጅ ሌላ የማያተርፍ! ማንኛውም ከመጥፎ ተግባርና ከወንጅል የማይከለክል ቂያም (የሌሊት ሶላት) ለባለቤቱ ከአላህ መራቅ እንጂ ሌላን አይጨምረውም፤ እንደዚሁም ማንኛውም ከሐራም የማይከለክል ፆም ለባለቤቱ መጠላትንና መከልከልን እንጂ አይጨምረውም።
ሰዎች ሆይ! የአላህን ተጣሪ ሲሰሙ ፈጣን ምላሽ ከሚሰጡ፣ የአላህ አንቀፆች ሲነበቡላቸው ልባቸው ጥርት ከሚል ሰዎች፣ ሲፆሙ ደግሞ ምላሳቸው፣ ጆሯቸውና አይኖቻቻው ከሚፆሙ ሰዎች አኳያ እኛ የት ነው ያለነው? በነሱ ፈለግ ልንከተል አይገባምን? ያአላህ! ሁኔታችንን ወደ አንተ አቤት እንላለን፤ ያአላህ! እዝነትህን አደራ! ንግግሮች እያማሩ በሄዱቁጥር ስራዎች እየከፉ ሄዱ፤ ያ አላህ አንተ በቂያችንና መጠጊያችን ነህ!

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ