2013 ጁላይ 12, ዓርብ

ሶስት ቁልፍ መልዕክቶች

ሶስት ቁልፍ መልእክቶች

ቁልፍ 1: በቁርአን ውስጥ ስለ ረመዳን ጾም አህካሞች የተነገረበት ቦታ አንድና አንድ ብቻ ነው፥ እርሱም ሱረቱል በቀራ 185ኛው አንቀጽ:: ይሁንና ይህ አንቀጽ ሀተታውን የሚጀምረው ድሮ ጀምሮ የምናውቀውን አጀንዳ መልሶ በማውሳት ነው:: ይኸውም ቅዱስ ቁርአን ለሰው ልጆች ሁሉ መንገድ አመላካችና እውነትን ከሀሰት የሚለዩበት ደማቅ መመሪያ መሆኑን ነው:: ይህ ማለት ደግሞ ረመዳን በመጣ ቁጥር ከጾሙ እኩል ሊተገበር የሚፈለገው ጉዳይ ቁርአኑን እንደ አዲስ መተዋወቅና ለሌሎች ማስተዋወቅ ነው:: ረመዳን ማለት የምናውቃቸውን አያዎች ሳይቀር እንደአዲስ በግርምት የምንተዋወቅበት ልዩ አጋጣሚ ነው:: በተጨማሪም ሙስሊም ላልሆኑ ጎረቤቶች ከሳምቡሳና ሾርባ በላይ በስጦታ መልክ ልናበረክትላቸው የሚገባ ወደር የለሽ ሽልማትም ነው - ቅዱስ ቁርአን::

ቁልፍ 2
: ስለ ረመዳን ወር ሁኔታ ዝርዝር ሀሳብ ከተደመጠ በኋላ ቀጥሎ የሰፈረው መልእክት ደግሞ ዱአን የሚመለከት ነው:: ይታይህ እንግዲህ፥ ስለ ጾም ሲወሳ የማይታለፍ ርእስ ቢኖር የጾመኛ ሰው ዱአ ነው:: ቀደምት ሷሊሆች ለወጥ ማጣፈጫ ጨው ያጡ ለታ እንኳ ጎረቤት ከመበደር ይልቅ እጃቸውን ማንሳት ይቀላቸው ነበር:: የገባንበት አስቸጋሪ ፈተና በሱጁዶች ውስጥ ከሚደረጉ ዱአዎች ጋር ሲነጻጸር የትንኝ ክብደት አያህልም:: የኡማው የዘወትር ድል የተጠራቀመውም እዚሁ ወር ላይ በሚሰሙ ዱአዎች ውስጥ ነውና በባዶ መጨነቃችንን ትተን ዱአችንን እንያያዘው::

ቁልፍ 3
: ቀጣዩ አያ ደግሞ ስለ ቤተሰብ ጉዳይ ያነሳል:: ወንድና ሴት እርስ በእርስ የሚሸፋፈኑ ጥንዶች መሆናቸው በመጥቀስ ይህንን የድል ወር ወንዶች ከሴቶች ላይ ሴቶችም ከወንዶች ላይ ሊኖሩ የሚችሉ ነውሮችን እንዲሁም የስራ ጫናዎችን መሸፋፈን፣ መከፋፈል እንዳለብን ይጠቁማል:: በረመዳን ውድ ግዚያቶች ላይ ሴቶች ቱርክ ፊልም ላይ የሚታዩ ምግቦችን የሚለማመዱበትና ወንዶች ደግሞ ቁርአንን ሺ ግዜ የሚደጋግሙበት ልማድ መታደስ አለበት:: ረመዳኑ የቁርአን፣ ረመዳኑ የዱአ፣ ረመዳኑ የለይል ሶላት እንጂ ረመዳኑ የ "ጣሽ መጣሽ" እና የምግብ ትምህርት ቤት እንዳይሆን ልዩ ትኩረት ይደረግ!

2013 ጁን 26, ረቡዕ

መልካም የሆነ ማኀበራዊ ትስስር

መልካም የሆነ ማኀበራዊ ትስስር

በመተባበር ላይ የተመሠረተ መተዛዘንና የሰፈነበት ሕዝባዊ ትስስር መፍጠር የደስታን መንፈስ ስቦ የማምጣት አቅም አለው
እንዲህ ዓይነት የሲቨል ተቋማት በኢስላም ወርቃማ ዘመን ብልጭ ብለው ከጠፋ ወዲህ በየትም ሀገርና
በየትኛውም ሥርዓት ደግም ለመከሰት አልበቁም ጠንካራ የሙስሊሞች ማኅበረሰብ የጠንካራ እምነት ፍሬ እንጂ ሌላ ምን ሊሰኝ ይችላል!?

... ያ ትውልድ በርግጥ ፈጣሪው በነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በኩል መልዕክት ላከለት እርሱም ያለማቅማማት ወዶ ተቀበለ::
በዚህም የሥልጣኔ ቁንጮ ሆኖ በታሪክ ዓምዶች ላይ አንፈራጠጠ፤ የዚህ ሁሉ የመጨረሻ ውጤት ደስታና ብልፅግና መሆኑ እዚህ ላይ ሊሰመርበት ይገባል::
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
<<የአማኞች ሁኔታ ሕንፃውን እንደተሠራበት ጡብ ነው አንዱ ሌላውን በመደገፍ ሕንፃውን ያቆሙታል>> (ኢማሙ ቡኻሪና ሙስሊም)
<<የምመእናን እርስ በርስ መደጋገፍና መተዛዘን አምሳያው እንደ አንድ አካል ነው
ከአካላችን ውስጥ አንዱ ጣታችን ቢታመም መላው ሰውነታችንም አብሮ ይታመማልና>> (ቡኻሪና ሙስሊም)
<<ከናንተ አንዳችሁ ለራሱ የሚወደውን ነገር ለወንድሙ እስካልወደደ ድረስ አላመነም>> (ቡኻሪና ሙስሊም)

አንድ መስሊም በሌላ ሙስሊም ወንድሙ ላይ የሚከተሉት ግዴታዎች ይፀኑበታል
1. ስትገናኙ ስላምታን መለዋወጥ (ይኸውም የአላህ ስላም ባንተ ላይ ይሁን የሚለውን ነው)
2. ቢጋብዝህ ግብዣውን መቀበል
3. ምክር እንድትለግሰው ቢጠይቅህ በሐቅ ላይ ሆነህ ከልብህ ምከረው
4. ቢያስነጥሰውና አላህን ቢያመሰግን አላህ ይዘንልህ (ይማርህ) በማለት ዱዓ አድርግለት
5. ሲታመም ጠይቀው
6. ሲሞት አስክሬኑን ሽኝ (ቅበረው) (ኢማም ሙስሊም)

<<በአላህ በፍርዱ ቀን ያመነ ሰው በጎረቤቱ ላይ መጥፎ ድርጊት አይፈጽም
በአላህ ና በመጨረሻው ቀን ያመነ እንግዳውን ያክብር
በአላህ በፍርዱ ቀን ያመነ በጎ ነገር ይናገር ወይም ዝም ይበል>> (ቡኻሪና ሙስሊም)
በማለት እንደ ማር ጠብታ የሚጣፍጥ ምክራቸውን አንቆርቁረውልናል::
ሁለተኛው የኢስላም ኸሊፋ ዑመር ቢን አል-ኸጧብ (ረ.ዐ) ለሁሉም
ሰው በበቂ ሁኔታ እስኪዳረስ ድረስ ቅባት ያለው ነገርና ሥጋ ላለመመገብ ወስነው ነበር::

እንዲህ ያለው በሥነ-ምግባር አንፃር በዓለም ላይ ከታዩ ህዝቦች ሁሉ ቁንጮ የሆነ ማኀበረሰብ አንዱ ለሌላው ወንድሙ ሲል የራሱን ጥቅም አሳልፎ በመስጠት በመዋደድና በመላላቅ የደስታን ባሕር በቁጥጥሩ ሥር አድርጎ እንደፈለገ ሲቀዝፍና ሲዋኝበት መኖሩ አያስደንቅም!?

የረመዳን ወር የትኩረት አቅጣጫዎች

የረመዳን ወር የትኩረት አቅጣጫዎች

1. ልቦናዎች የሚደብቁትን ሁሉ የሚያየውና የሚያውቀው አላህ (ሱ.ወ) የኢማናችንን ጥንካሬ በዚህ ፆም ሊፈትነን እንደፈለገ በመገንዘብ ከፍተኝ ትኩረት መስጠት፤
2. ረመዳንን ስንፆም በኒያ (አስበንና ወስነን) መሆን አለበት፤ ምክንያቱም ያለ ኒያ የፆመ ሰው ምንዳ የለውምና።
3. ቀኑን በሙሉ በመኝታ ከማሳለፍ መቆጠብ አለበን።
4. ቁርኣንን ከሌላው ጊዜ በተሻለ በብዛት መቅራት አለብን።
5. ከፈጣሪያችን ጋር ተውባ (ወደሱ መመለስ) ማደስ ያስፈልጋል።
6. የረመዳንን ሌሊቶች በጫወታና ጠቃሚ ባልሆኑ ነገሮች ከማሳለፍ መቆጠብ አለብን።
7. በረመዳን ወር ዱዓ፣ ከአላህ ማህርታ መጠየቅና ወደሱ መዋደቅ ማብዛት አለብን።
8. አምስት ወቅት ሶላቶችን በመስጂድ ጀመዐ ጠብቀን መስገድ ያስፈልጋል።
9. ሙሉ አካላችን አላህ (ሱ.ወ) ከከለከላቸው ነገሮች በመቆጠብ መፆም ይኖርባታል።

ቁርኣን የወረደበት የረመዳን ወር ይህ ነው፤ ይህ ወር ከጀነት የሚቀረብበትና ከእሳት የሚራቅበት ጊዜ ነው። እድሜህን ሁሉ ያለ ኢባዳ ያባከንክ፣ በረመዳንና በሌላውም ጊዜ ከኢባዳ ወደ ኋላ የቀረህ፣ዛሬ ነገ እያልክ በቀጠሮ ወደ አላህ መመለስን ያዘገየህ፣ ረመዳንንና ቁርኣንን በቸልተኝነት እያለፍክ ያለህ ሰው ሆይ! እስኪ በአላህ ይሁንብህ ንገረኛ እስከመቼ በንዲህ አይነት ህይወት ትቀጥላለህ? አይቀሬው ሞት ድንገት ከተፍ ቢል ጌታህፊት ምን ይዘህ ትቀርባለህ?... ከወዲሁ ቆም ብለህ ልታስብበት ይገባል!

በተከበረው ረመዳን ከምግብ ብቻ ተከልክለህ አይንህን፣ አንደበትህንና አጠቃላይ ውሎህን ያልገራሀው ወንድሜ ሆይ! ድካምህ በከንቱ እንዳይቀር እያሰብክበት ነውን? ስንት ፆመኛ አለ ከፆሙ ራሀብንና ጥምን እንጅ የማያተርፍ! ስንት ሰጋጅ አለ ከሶላቱ እንቅልፍ ማጣትና ድካምን እንጅ ሌላ የማያተርፍ! ማንኛውም ከመጥፎ ተግባርና ከወንጅል የማይከለክል ቂያም (የሌሊት ሶላት) ለባለቤቱ ከአላህ መራቅ እንጂ ሌላን አይጨምረውም፤ እንደዚሁም ማንኛውም ከሐራም የማይከለክል ፆም ለባለቤቱ መጠላትንና መከልከልን እንጂ አይጨምረውም።
ሰዎች ሆይ! የአላህን ተጣሪ ሲሰሙ ፈጣን ምላሽ ከሚሰጡ፣ የአላህ አንቀፆች ሲነበቡላቸው ልባቸው ጥርት ከሚል ሰዎች፣ ሲፆሙ ደግሞ ምላሳቸው፣ ጆሯቸውና አይኖቻቻው ከሚፆሙ ሰዎች አኳያ እኛ የት ነው ያለነው? በነሱ ፈለግ ልንከተል አይገባምን? ያአላህ! ሁኔታችንን ወደ አንተ አቤት እንላለን፤ ያአላህ! እዝነትህን አደራ! ንግግሮች እያማሩ በሄዱቁጥር ስራዎች እየከፉ ሄዱ፤ ያ አላህ አንተ በቂያችንና መጠጊያችን ነህ!

ውበት (ጥበብ) በኢስላም መነጽር


ውበት (ጥበብ) በኢስላም መነጽር

ኢስላም በራሱ ውበት ነው፡ ጥበብ ነው አላህም ቆንጆ ነው ቆንጆ የሆኑ ነገሮቸን ይወዳል በሃዲስ ላይ ረሱላቸን እንዳሰፈሩትማለት ነው “.. إن الله جميل يحب الجمال ..” የሰው ልጅም በተፈጥሮው በውበትና በጥበብ እንዲማረክ አድርጎ ነው አላህ የፈጠረው በተቃራኒው ደግሞ ውበት የሌላቸውን ነገሮቸ ይጠላል ማለት ነው።
ውበትን (ጥበብን) በኢስላም መነጥር ስንመለከተው አካላዊ ቅርጽ ብቻ አደለም ያለው መንፈሳዊ ውበትም አለ። ለዚህም ነው ረሱል ( ) ሰዎቸ ሴትን ልጅ ለትዳር... የሚከጅሏት 1_ ለውበቷ 2_ ለሃብቷ 3_ ለዘሯ 4_ ለዲኗ (እምነቷ) መሆኑን ከጠቀሱ በኋላفاظفر بذات الدين ....” “ባለዲኗን አደራነው ያሉት ምክንያቱም ውበት ለብቻው ያለ እሴት፡ ያለኢማን ባዶ
ቀፎ ነውና።
ንግግርም ቢሆን ቆንጆና መጥፎ አለውوقولوا للناس حسنىለሰዎቸ መልካሙን ተናገሩበማለት በቁርአን ላይ የታዘዝነው
ግጥም ጥበብ ነው ነገር ግን ሁሉም የግጥም አይነት አይደለም ረሱላቸንም ( ) እንዲህ ብለዋል <        متفق عليه  وقبيحه قبيح  حسنه حسن الشعر كالكلام     > ግጥም እንደማንኛውም አይነት ንግግር ነው ፡ጥሩው ጥሩ ሲሆን መጥፎው ደግሞ መጥፎ ነው

አንድን ነገር ጥሩ ወይም መጥፎ ብለን የምናስቀምጥበት ሚዛናቸን ደግሞ ኢስላም ነው አለበለዚያ ወደ አንጻራዊ ንድፈ ሃሳብ (the theory of relativity) ልናመራ ነው ይህ ደግሞ ኢስላም ወደማይፈልገው መንገድ ሊያመራን ነው ለምሳሌ፡ ሴት ልጅ ሰውነቷን ገላልጣ ለፋሸን ሾው ወይም ለዳንስ ትርኢት ራሷን መጋበዟን አንዳንዶቹ እንደ አርት ሊወስዱት ይቸላሉ በኢስላም መነጥር ግን ዝቅጠት እንጂ ሌላ አደለም
በጥቅሉ አንድ ሙስሊም ነኝ የሚል ሰው የአኗኗር ዘይቤው በኢስላም አስተምህሮት ላይ የተመረኮዘ መሆን አለበት በግል ህይወቴ ላይ ሃይማኖት ጣልቃ ሊገባብኝ አይገባም ማለት (secularism) ርእዩት እንጂ የኢስላም አደለም ኢስላም ሁሉ ነገራቸን ላይ ጣልቃ ይገባል መስገድና መጾም ብቻማ ከሆና ኢስላምን ከሌላው ሃይማኖት ምን ለየው?!
قل إن صلاتي ونسكي ومحياي ومماتي لله رب العالمين...”
በል ስግደቴ አምልኮቴ መኖሬም መሞቴም ለአለማቱ ጌታ አላህ ነው የምትለውም የቁርአን አንቀጽ መልእክት ይኸው ነው
አላህ ህይወታቸንን በሙሉ ለርሱ እንድናደርግ ያግዘን አሜን!